የፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በድጋሚ መመረጥ አገሪቱ የጀመረችውን ልማት ያጠናክራል
አሶሳ መስከረም 29/ 2000/ዋኢማ/ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በድጋሚ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው አገሪቱ በልማትና በውጭ ግንኙነት በኩል የጀመረችውን መልካም ሂደት የበለጠ እንደሚያጠናክረው አንዳንድ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት አሰግድ መላኩና ወጣት ሰኢዳ ከድር በሰጡት አስተያየት፣ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በድጋሚ መመረጣቸው ባካበቱት ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ልምድ የአገሪቱን መልካም ገጽታ ለውጭ አገር በማስተዋወቅና የተጀመሩ ልማቶችን ለማፋጠን ያግዛል።
መምህር ዮሀንስ ዲንቃና አቶ አበራ አዱኛ በበኩላቸው፤ፕሬዝዳንቱ በተለይም እንደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ባሉና በልማት ወደኋላ የቀሩ ክልሎችን በተደጋጋሚ በመጎብኘት የሰጡት ትኩረት ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች በእኩል ዓይን እንደሚያዩ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ወይዘሮ ከድጃ መሀመድና አቶ ታደሰ ገበየሁ የተባሉ የከተማዋ ኗሪዎችም ፕሬዚዳንቱ ኤችአይቪ/ኤድስን በመከላከል፣ የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት መልሶ እንዲተካ ለማድረግ ያደረጉት አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ፣ በድጋሚ መመረጣቸው በቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት በአገሪቱ ሰላም እንዲጠናከርና የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲጎለብት ያደርጋሉ የሚል እምነት እንዳላቸው መግለፃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። (http://www.waltainfo.com/AmNews/2007/Oct/10Oct07/37179.htm)
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment